የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን የስንቅሌ ቆርኬዎች መጠለያን የ10 ዓመት የስርዓት አያያዝ እቅድ ሰነድን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በሀዋሳ ከተማ ሴንትራል ሆቴል ታህሳስ 17/2013ዓ.ም አፀደቀ፡፡

እንደሚታወቀዉ የስንቅሌ ቆርኬዎች መጠለያ የአስር አመት ስርዓት አያያዝ እቅድ ሰነድን በተለያዩ ጊዜያት ከተቋሙ እና ከሌሎች አጋር አካላት ጋር ኮሚቴዎችን እና በዘርፉ ልምድ ያካበቱ ባለሞያዎችን በማዋቀር ማህበረሰቡን፣ በማሳተፍ መካተት ያለባቸውን ጉዳዮች በማካተት ሲሰራ ቆይቷል፤ በእለቱመም የተሰራውን የመጠለያው የስርአት አያያዝ እቅድን የአገር ሽማግሌዎች /አባገዳዎች ፣የማህበረሰብ ተወካዮች ፣የዞንና የወረዳ አመራሮች እንዲሁም የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች እና ሰራተኞች በተገኙበት ፀድቋል፡፡

በእለቱም የኢትዮጵጣ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ እና የስንቅሌ ቆርኬዎች መጠለያ ቺፍ ዋርደን አቶ ደስታ በዳሶ ከአባ ገዳዎች መልእክትና ምርቃት በመቀጠል መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በመልእክታቸውም መጠለያዉ በልዩ ትኩረት የስዌይን ቆርኬዎችን ከጥፋት በመጠበቅና በማልማት ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍና በቱሪስት መስህብነት ለጎብኚዎች አገልግሎት በመስጠት ከዘርፉ ሊገኝ የሚችለውን ገቢ በማሳደግ ለሀገራዊ ኢኮኖሚ ብሎም ከአዋሳኝ ማህበረሰብ ልማት የራሱን አስተዋፅኦ እንዲያበረክት ማስቻል መሆኑ እና በዚሁ አግባብ የስንቅሌ ቆርኬዎች መጠለያን የስርዓት አያያዝ እቅድ ዝግጅት አለም አቀፍ ደረጃን ባማከለ መመሪያ መሰረት ሲዘጋጅ ቆይቶ በዛሬው እለት የመጨረሻ ረቂቅ የሆነው ሰነድ ዋና ዋና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ተጨማሪ ግብአቶችን በማካተት ለማፅደቅ ይህ የምክክር መድረክ አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

እንዲሁም ዋና ዳይሬክተሩ ተሳታፊውን በማወያየት እና ገንቢ አስተያየት ብሎም ማስተካያ ሀሳብ ካለ በማከል የማይተካ ሚናችሁን እንደምታበረክቱ ፅኑ እምነት አለኝ በማለት ይህንን የ10 ዓመት እቅድ የመጠለያው ሁለንተናዊ የለውጥ መመሪያ አድርገን ለትግበራ ወጥ የሆነ መረዳት ኖሮን ወደ ትግበራ ከገባን ረጅም በማይባል ጊዜ ያሰብነውን ግብ ማሳካት እንደምንችል እምነቴ የፀና ነው በማለት እና ሰነዱን በማፀደቅ አጠናቀዋል፡፡

ኢ.ዱ.ል.ጥ.ባ
ታህሳስ 17/2013ዓ.ም
ሀዋሳ

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.